የአውሮፓ ህብረት ለምስራቅ አፍሪካ ተረጅዎች 165 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ሊሰጥ ነው፤

መጋቢት 12፣2009 ዓ.ም.

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት የአውሮፓ ህብረት አለም አቀፍ ትብብር እና ልማት ኮሚሽነር ኔቨን ሚሚካ የአውሮፓ ህብረት በአፍሪካ ቀንድ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ለተራቡ ዜጎች የሚደርስ 165 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ሊሰጥ መሆኑን አስታወቁ፡፡

በአስቸኳይ የሚያስፈልገውን እርዳታ እና ድጋፍ በማድረግ የሰዎችን ህይዎት ማዳን ያስፈልጋል ብለዋል ኮሚሽነር ሚሚካ።

የአሁኑ ድጋፍ ህብረቱ ከዚህ ቀደም ቃል ከገባው ውጭ የተሰጠ መሆኑ ታውቋል፡፡ በድጋፉ የሶማሊያ እና የደቡብ ሱዳን ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

ህብረቱ ከሚሰጠው ድጋፍ 1መቶ ሚሊዮን ዩሮ የሚሆነውን በደቡብ ሱዳን ለተከሰተው ቀውስና ከአገሪቱ ወደ ጎረቤት አገራት ለተሰደዱ ስደተኞች ጊዜያዊ መፍትሔ የሚውል ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም በሶማሊያ፣ ኬኒያ እና ኢትዮጵያ ለተከሰተው የድርቅ አደጋ 65 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡን የህብረቱ የሰባዊ ተራድኡ እና ቀውስ ማኔጅመንት ኮሚሽነር ክሪስቶስ ስታይልአያንደስ ገልጸዋል።

የአውሮፓ ህብረት ባለፈው ዓመት ለቀጠናው ድጋፍ የሚውል አራት መቶ ሚሊዮን ዩሮ መድቦ በድርቅ ለተጎዱ የቀጠናው አካባቢዎች ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው።