Back

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራዓተ-ጾታ አካቶ ስልጠና ሰጠ፤

የካቲት 7፣ 2009 ዓ.ም.  

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ጉዳይ ጽ/ቤት ከመስራያ ቤቱ የሰው ሀብት ልማት ዳይሬክቶሬት ጄኔራል እና የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የስርዓተ-ጾታ ልማት ክፍል ጋር በመተባበር በሶስት ዙር የሚጠናቀቅና የመስርያ ቤቱን ሰራተኛና አመራር የሚያሳትፍ ስልጠና አዘጋጀ።

ስልጠናው ባለፉት ስድስት ወራት ከሥራዓተ-ጾታ አካቶ (Gender Mainstreaming) ጋር በተያያዘ በመስርያ ቤቱ የነበረውን አፈጻጸም በመገምገም የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት የተዘጋጀ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ጉዳይ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬህይወት አስራት ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ የሥራዓተ-ጾታ አካቶ ስራዎች በመስሪያ ቤቱ አብዛኛው የሥራ ክፍሎች ተግባራዊ አለመሆናቸውን ገልጸው፤ እያንዳንዱ የሥራ ክፍል በሚቀጥለው ግማሽ የእቅድ በጀት ዓመት የሚያደረገውን ክንውን የሥራዓተ-ጾታ አካቶ ስራዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆን እንደሚገባው አሳስበዋል።

በ2008 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ በሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በተደረገው ግምገማ፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግንዛቤ ከመፍጠር አንጻር የተሻለ ሚኒስቴር መስራያ ቤት የነበረ መሆኑን፣ ነገር ግን ተግባራዊ ማድረግ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ግምገማው እንደሚያመላክት አስታውሰው፤ ስልጠናው ከግንዛቤ ማስጨበጥ ባሻገር ወደ ተግባርና ተጨባጭ ለውጥ ለመግባት እያደረግን ላለነው እንቅስቃሴ ይረዳል ብለዋል ዋና ዳሬክተሯ።