Back

የዩጋንዳው ፕሬዝዳንት በደቡብ ሱዳን የተከሰተውን ግጭት ለማስቆም ውይይት ያስፈልጋል አሉ፤

መጋቢት 13፣ 2009 ዓ.ም.

የዩጋንዳው ፕሬዝዳንት የወሪ ካጉታ ሙሰቨኒ በደቡብ ሱዳን ያለውን ግጭት ለመፍታት በጦር ሜዳ ያሉ አካላት ወደ ድርድር መመለስ አለባቸው አሉ።

ፕሬዝዳንቱ ጦርነት ችግሩን ሊፈታው እንደማይችል አስረግጠዋል።  የጦርነቱ ተሳታፊ አንጃዎች ሁለት አብይ ጉዳዮችን ለማሳካት ማለትም ምርጫ ለማካሄድ እና የደህንነትና ጸጥታ ዘርፉን ለማሻሻል ድርድር ማድረግ አለባቸው ሲሉ ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል።

ባለፈው አርብ ከቻይና መንግስት የአፍሪካ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ ጋር ውይይት ያደረጉት ፕሬዝዳንት ሙሰቨኒ በደቡብ ሱዳን ያለውን ችግር አይዲዮሎጃዊ ሲሉ ፈርጀውታል። በደቡብ ሱዳን ያሉ ቡድኖች ህዝባቸውን ለማስተዳደር የሚያስችል ግልጽ የሆነ አመራር የላቸውም ብለዋል ፕሬዝዳንቱ አክለው። ‘'በዚህም ምክንያት የውሸት አይዲዮሎጂ በሆነው የጎሳ ክፍፍል ህዝቡ እንዲገፋ በማድረግ ደህንነቱን አደጋ ላይ ጥለዋል። ኃይል ለግጭቱ እልባት ሊያመጣ አይችልም።''